Numbers 12

ማርያምና አሮን ሙሴን ተቃወሙ

1ሙሴ ኢትዮጵያዊት ሴት አግብቶ ነበርና ባገባት ኢትዮጵያዊት ምክንያት ማርያምና አሮን ይነቅፉት ጀመር። 2እነርሱም፣ “ለመሆኑ እግዚአብሔር (ያህዌ) የተናገረው በሙሴ አማካይነት ብቻ ነውን? በእኛስ አልተናገረም?” ተባባሉ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ይህን ሰማ።

3ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር።

4ወዲያው እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ አሮንንና ማርያምን፣ “ሦስታችሁም ውጡና ወደ መገናኛው ድንኳን ኑ” አላቸው፤ ሦስቱም ወጥተው ሄዱ። 5ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ዐምድ ወረደ፤ በድንኳኑም ደጃፍ ቆሞ አሮንንና ማርያምን ጠራቸው፤ ሁለቱም ወደ እርሱ በቀረቡ ጊዜ፣ 6እንዲህ አላቸው፤ “ቃሌን አድምጡ፤

የእግዚአብሔር (ያህዌ) ነቢይ በመካከላችሁ ቢኖር፣
በራእይ እገለጥለታለሁ፤
በሕልምም እናገረዋለሁ።
7ለአገልጋዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤
እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።
8እኔ ከእርሱ ጋር የምነጋገረው ፊት ለፊት ነው፤
በግልጽ እንጂ በልዩ ዘይቤ አይደለም፤
እርሱ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልክ ያያል።
ታዲያ እናንተ አገልጋዬን ሙሴን
ትቃወሙ ዘንድ ለምን አልፈራችሁም?”
9 የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እርሱም ትቷቸው ሄደ።

10ደመናው ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ፣ እነሆ፤ ማርያም በለምጽ
በዕብራይስጡ ትርጕም ለምጽ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የቈዳ በሽታዎችንም ያመለክታል።
ተመታች፤ እንደ በረዶም ነጣች። አሮንም ወደ እርሷ ዘወር ሲል ለምጽ ወርሶአት አየ፤
11ሙሴንም እንዲህ አለው፣ “ጌታዬ ሆይ፤ በስንፍናችን የሠራነውን ኀጢአት እባክህ አትቍጠርብን። 12እርሷንም በእናቱ ማሕፀን ሳለ ሞቶ ግማሽ አካሉ ከተበላ በኋላ የተወለደ ጭንጋፍ መስላ እንድትቀር አታድርግ።”

13ስለዚህም ሙሴ፣ “አምላክ (ኤል) ሆይ፤ እባክህ ፈውሳት” ብሎ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ።

14 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለሙሴ፣ “አባቷ እፊቷ ላይ ቢተፋባት እስከ ሰባት ቀን በኀፍረት መቈየት አይገባትምን? አሁንም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን እንድትገለል አድርግ፤ ከዚያ በኋላ ግን ልትመለስ ትችላለች” ሲል መለሰለት። 15ስለዚህም ማርያም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ተገለለች፤ ከዚያ እስክትመለስም ሕዝቡ ጕዞውን አልቀጠለም ነበር።

16ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተነሣ፤ በፋራን ምድረ በዳም ሰፈረ።

Copyright information for AmhNASV